ማሠልጠኛው የተመሰረተበትን ፳ኛ ዓመት በዓል ከሰኔ ፯ – ፱ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ተከብሮ ውላል
ሥልጠናውን ሲጀመር ከፄዴንያ ስመኝ ማርያም ገዳም ጋር በመተባበር በገዳሙ ጽ/ቤት የተከናወነ ሲሆን፤ አዳራቸውና ምግባቸው በዘመናዊ ትምህርት ቤታችን በእንጨት ከተሠራ ተደራራቢ አልጋ ወደ ብረት አልጋ እስኪለወጥ ለሦሰት ዓመት ቀጥሎ ነበር፡፡
ከአንድነት ኑሮው ዓላማ አንዱና ዋናው የሆነውን “በኢ.ኦ.ተ. ቤተክርስቲያን ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በሚደረገው አገልግሎት ለቤተክርስቲያን እድገትና ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት” የሚለውን ተግባራዊ ለማድረግ አባላት ተስማምተው ያጸደቁት ደንብ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት በማቅረብ የሰባክያነ ወንጌል ፈቃድ ሐምሌ ፪(2) ቀን ፲፱፻፺፭(1995) ዓ.ም. አግኝቷል፡፡ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ ይህንን ፈቃድ ለማግኘትና ደቀመዛሙርቱን በማሠልጠን ተግባር በጤንነታቸው ብቻ ሳይሆን በከባድ ሕመም ውስጥ እያሉ ሥርዓተ ትምህቱን በመቅረጽና ሠልጣኞችን በማስተማር ያደረጉት አስተዋጽኦ ለዚህ ማሠልጠኛ የማይረሳ የታሪክ ዓምድ ነው፡፡
ማሠልጠኛው “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጽርሐ ጽዮን አንድነት አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን የሰባክያነ ወንጌል ማሠልጠኛ ማዕከል” ተብሎ ይጠራል፡፡
በትንቢተ ሆሴዕ “ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል፡፡”(ሆሴዕ ፬÷፯ ) እንዲሁም በግብረ ሐዋርያት ኢትዮጵያዊው ጃንደረባው “የሚመራኝ ሳይኖር ይህን እንዴት ለማወቅ ይቻለኛል?” ብሎ እንደጠየቀ(የሐዋርት.ሥራ ፰÷፴፩) ምላሽም እንዳገኘ፤ የአንድነት ኑሮው የገጠሪቱን ቤተክርስቲያን በኅብተሰቡ ቋንቋ የሚያስተምሩ የሰባክያነ ወንጌልን አጥረት ለማቃለል፤ የማሠልጠን ሥራ የጀመረው በ፲፱፻፺(1990) ዓ.ም. ክረምት ሲሆን፤ በወቅቱ በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ብዙ አብያተክርስቲያናት በአገልጋይ እጦት እየተዘጉ፣ ምእመናንም ጠባቂ፣ እረኛ’ መምህር በማጣት በመናፍቃን እየተነጠቁ ስለሆነ፤ የማኅበረችንን የልጅነት ድርሻ ለመወጣት ባለን ዘመናዊ ት/ቤት በክረምት ሲዘጋ ሰባክያነ ወንጌል የማሠልጠኑ ሥራ ተጀምሯል፡፡