“የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።” (፪ኛ ቆሮ ፲፩፥፪)

የኛን ኃጢአትና ድካም ሳይመለከት ቸር አምላክ በሕይወት ጠብቆ እርሱ ቢፈቅድ ብለን ጥቅምት ፯ ቀን ለማከናወን እቅደን የነበረውን የሰባኪያነ ወንጌል የምረቃ በዓል ለማክበር ስላበቃን ለጌትነቱ የሚገባውን ምስጋና በማስቀደም፤ በሀገር ውስጥና በውጪ ይህን መልእክት የምትከታተሉ እናንተም፤ በጸሎታችሁ፣ በእውቀታችሁ፣ በገንዘባችሁ ድጋፋችሁ እንዳይለየን ያቀረብነውን ጥያቄ ተቀብላችሁ፤ ለዚህ ውጤት እንድንበቃ የተባበራችሁን ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ለወርኃ ጽጌ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ እንላለን፡፡

በጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ አንድነት ኑሮ የሰባኪያነ ወንጌል ማሠልጠኛ ማዕከል፤ የዛሬ ተመራቂዎችን ሳይጨምር፤ በ፴፪ ዙር ሥልጠና ከ፶፮ አህጉረ ስብከት የገጠሪቱ አብያተክርስቲያናት ተመርጠው የመጡና ተመልሰው ፸፮ የኅብረተሰቡ ቋንቋ ማስተማር የሚችሉ ፩ ሺህ ፯፵፱ ደቀመዛሙርት ሠልጥነው ተመርቀዋል፡፡

በዘንድሮው የክረምት ሥልጠና ምንም እንኳን በኮቪድ 19 ወረርሽኝና ልዩ ልዩ ስጋቶች ምክንያት በታቀደው ዕቅድ መሠረት፤ በርከት ያሉ ደቀመዛሙርትን እንዲሁም የዲያቆናት ሥልጠና ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ አምጥቶ ማስተማር ባይቻለም፤ በ፳፻፲፪ ዓ.ም ብፁዕ አባታችን አቡነ ናትናኤል በዓይነቱ ለየት ያለ በሚኒሊየም አዳራሽ ባዘጋጁት ጉባኤ ላይ፤ ከምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በአፋን ኦሮሞ ቃለ ወንጌልን ለሚያስተምሩ ፷(ስድሳ) ሰባኪያነ ወንጌል ለማሠልጠን ቃል በገባነው መሠረት ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ በበጋው ፷(ስድሳ) ሰባኪያነ ወንጌል ለአራት ወራት ሠልጥነው የተመረቁ ሲሆን፤ በአሁኑም የ፴፫ኛ ዙር ክረምት ሥልጠናም ከዚሁ ከምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ከ፲፰ ወረዳዎች ከተውጣጡ ካህናት፣ዲያቆናትና የሰ/ት/ቤት ወጣቶችን ያካተተ ፴(ሠላሳ) ደቀመዛሙርት ከሐምሌ ፩ ጀምሮ ለሦስት ወራት በአፍን ኦሮሞ በተጨማሪ በአማርኛ ሥልጠናውን ተከታትለው፣ በመኸሩ ሥራ ለመሳተፍ አስፈላጊውን የሃይማኖት ትጥቅ ይዘው ተሸኝተዋል፡፡

እነዚህ ተመራቂዎች ከምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት ከ፲፰ ወረዳዎች ተመርጠው የመጡ ሲሆን፡፡ ወደ መጡበት ቦታ ሲመለሱ በአፋን ኦሮሞና በአማርኛ ቋንቋ ማስተማር የሚችሉ ናቸው፡፡ እስከ አሁን በነበሩበት አካባቢ በቅስና ፬ ፣ በዲቁና ፲፪፣ ከበሰንበት ት/ቤት ፲፬ ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በቀሪው ዘመናቸው ደግሞ ምእመናን የሆኑት ክህነትን ተቀብለው ከስብከት ጋር አጣምረው ለቤተ ክርስቲያናችን አለኝታ ይሆናሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
በተጨማሪ በጽርሐ ጽዮን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር ከሰበካ ጉባኤው በተጻፈላቸው የትብብር ደብዳቤ መሠረት ከሚያዚያ ወር ፳፻፲፫ ዓ.ም እስከ ነሐሴ ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ድረስ አምስት አይነት መሠረታዊ ትምህርቶችን በመከታተል ለሕይወታቸው መንፈሳዊ ጥንካሬ እንዲሁም ለሚጠይቋቸው መልስ ለመመለስ መንገድ የሚሆናቸውን እውቀት በመቅሰም በዛሬው ዕለት ከብፁ አባታችንን ቡራኬ ተቀብለው ተመርቀዋል።

ከሀገር ውስጥና ውጪ ተባባሪ አባላት፣ ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች የ፳፻፲፫ ዓ.ም የማልጠኛው ገቢ ሂሳብ ብር 1,491,913.50 ሲሆን፤ ከዚህ ላይ ብር 981,715.9 ወጪው ሆኗል። የዚህ ዓመት የገቢና ወጪ ሒሳብ በየዓመቱ እንደሚደረገው ሁሉ በባለሙያ ተሠርቶ በውጪ ኦዲተር እንዲመረመርና ፈቃዱ እንዲታደስ ለማድረግ በሒደት ላይ እንገኛለን።

የኑሮ ውድነትና የሥጋ ፈቃድ ሳያሳሳችሁ፣ ገንዘብ ሳይተርፋችሁ፤ ጊዜያችሁንም ጭምርሽ የለገሳችሁት ይህ ሥጦታ፤ ደምን ከመለገስ የማይተናንስ ነውና፤ እግዚአብሔር በቸርነቱ መባችሁን ተቀብሎ፤ ረዥም ዕድሜ ከሙሉ ጤንነት ጋር እንዲሰጥልን ከልብ እንመኛለን፡፡

ለልዑል እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይግባውና የዚህ ማሠልጠኛ ሕልውና የተመሠረተው በእርሱ ቸርነት በምእመናን የጸሎት የሙያ የጉልበትና የገንዘብ ድጋፍ በመሆኑ፤ እስከ አሁን ከዚህ በላይ ለጠቀስናቸውና ላልጠቀስናቸው ለተደረገልን ዕርዳታ ሁሉ በቤተክርስቲያናችን ስም ልባዊ ምስጋናችንን እያቀረብን፤ ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ሥጦታቸውን ተቀብሎ፤ የኃጢአት መደምሰሻ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ፣ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ እንዲያደርግላቸው ከልብ እንመኛለን፡፡

በመጨረሻም በአሁኑ ጊዜ ጠላት ዲያብሎስ በብሔርና በቋንቋ ልዩነታችንን መጠቀሚያ አድርጎ፤ ካህናትና ምእመናን መሥዋዕትነት እንዲቀበሉ፣ የተረፉት እንዲሰደዱ፣ አብያተክርስቲያናት እንዲቃጠሉ እየተደርገ ነው።
እርስ በርስ ማጨካከኑ እንዲህ የከፋውም፤ ቀድመን በገጠሪቱና ጠረፋማው አካባቢ የሚገኘው ወገናችን፤ በቋንቋው ሃይማኖትና ሥነምግባር እንዲማር፣ እንደከተማው የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኝ ባለማድረጋችን ነው።
ከገጠሪቱና ጠረፋማው አካባቢ የተሻለ አገልግሎት በማግኘ ላይ የምንገኝ እኛ፤ በነፍስ ከቃለ እግዚአብሔር የተራቡትን፣ ጥምቀተ ክርስትና ስመ ውልድና ያላገኙትን፣ በባዕድ አምልኮ፣ በክህደትና በጥርጥር ያሉትን ወገኖቻችንን፤ ወደቀናችው መንገድ ወደ ሕገ ወንጌል ለመመልስ ” ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱና አስተምሩ ” ተብለን እንደታዘዝንው ሄደን ማስተማር ባንችል ሄደው የሚያስተምሩ ከአንድ ሰው ጀምሮ ለመስጠት የሚደረገውን አገልግሎት በሚቻለን ሁሉ ልንደግፍ ይገባል።

የልዑል እግዚአብሔር ፈቃዱ ቢሆን፤ በቀጣይ የበጋ ፴፬ኛው ዙር የ፳፻፲፬ ዓ.ም የአራት ወራት የሰባክያነ ወንጌል ሥልጠና ብዛት ፶ (ሃምሳ) እንዲሁም የአንድ ዓመት የአብነት ትምህርት ብዛት ፳(ሀያ) ካህናትና ፳ ዲያቆናት በአጠቃላይ ፺(ዘጠና) ደቀመዛሙርት ከየሀገረ ስብከቱ መጥተው እንዲማሩ ለማድረግ በታቀደው ሥልጠና የሁላችንም ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በድጋሚ በልዑል እግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን፡፡

ለበልጠ መረጃ
የአንድነት ኑሮው ዋና ጽ/ቤት
ቡራዩ ፄዴንያ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ የስልክ ቁጥር

+251-112-84-18-01 — +251-118-70-45-42 — +251-911-21-18-25 — +251-943-13-95-70 — +251-912-04-96-84
የፋክስ ቁጥር +251-112-84-35-83
ወይም በመለከት መጽሔት ዝግጅት ክፍል
ስልክ ቁጥር
+251-111-55-16-02 — +251-118-70-45-41 — +251-111-11-;8-73
website– http://www.tsirhatsion.com/
E-mail : eotc.tta.sbktwengmase@gmail.com
Facebook – f ጽርሐ ጽዮን

የመ.ሳ.ቁጥር 5490 አዲስ አበባ
አዲስ አበባ አራዳ (ፒያሳ) ደጎል አደባባይ አንበሳ ጫማ ቀጥሎ ባለው የድሮ ሕንፃ አንደኛ ፎቅ ውስጥ ከሚገኘው የመለከት መጽሔት ጽ/ቤት በማሠልጠኛው የባንክ ሒሳብ ቁጥር በቀጥታ ገቢ ለማድረግ
COMMERCIAL BANK OF ETHIOPIA
BURAYU E/O/T/B/K/YE/T/T/Z
Account፡ 1000102969972
ይህን የተቀደሰ ዓላማና ተግባር ቀጣይነት እንዲኖረው፤ በደብረ አሚን ተክለሃይማኖትና በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር አባላት አስተባባሪነት በአሜሪካን ሀገር የተቋቋምው የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ አንድነት ኑሮ ማኅበር በሚያደርገው የዕርዳታ ማስተባበር ተግባር ለመሳተፍ ይህ መልእክት በቴሌግራም ፣ በዋትስ አፕ ፣ በፌስ ቡክና በመሳሰሉት ማኅበራዊ ድህረ ገጾች የሚደርሳችህ ሁሉ ይህን መልእክትና ከዚህ ጋር የላክነውን ለአንድንት ኑሮው ቋሚ የገቢ ምንጭ በማቋቋም ከልመና ለማዳን፤ የጎፈንድ ሚ አድራሻ
gf.me/u/zpiib2
ለሌሎችም እንዲተላለፍ በማድረግ ትብብራችሁ አይለየን።
“አሁንም፥ ወንድሞቻችን ጸልዩልን፥ ወንጌል በእናንተ ዘንድ እንደተገለጠ ከሁሉ ደርሶ ይገለጥ ዘንድ ጸልዩ። ከክፉ ሰዎች ከዓላውያን እጅ እንድን ዘንድ። ሁሉ የሚያምን አይደለምና።”
(፪ኛ ተሰሎንቄ ፫፥፩-፪)

እንኳን ደስ አላችሁ !