ማኅበሩ ከአምስቱ ዓላማዎቹ አንዱ የሆነው “የተቸገሩትን ወገኖች መርዳት” የሚለውን ተግባራዊ ለማድረግ በራሱ ስፍራ ከመጀመሩ በፊት በሰፈረበት አጥቢያ ባለችው የፄዴንያ ስመኝ ቅ/ ማርያም ገዳም ከ 1986 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1992 ዓ.ም. በዓመት ሁለት ጌዜ 70 ለሚሆኑ ተረጂዎች 25 ኪሎ ስንዲና ልዩ ልዩ ልብሶች በመስጠት ምንም ገቢ የሌላቸውን ወገኖች ቤት ለቤት በመሄድና በመመዝገብ የበጎ አድራጎት ስራውን ጀምሯል።

ረጂዎቹ ስጦታቸውም በማኅበራችን አባላት አሳሳቢነት ከአሜሪካን ዲሲ ቅ/ ማሯም ቤ/ክና ከገዳመ ተክለሃይማኖት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ፤ በወ/ሮ ፋሲካ አሥራት አስተባባሪነት በየዓመቱ ለልደትና ለፋሲካ ከአራት መቶ ዶላር ያላነሰ ገንዘብ እንዲሁም ከቦሌ ማተሚያ ቤት የኪዳነምሕረት ጽዋ ማኅበር ፤ ከጂንአድ ሠራተኞች የማኅበረ ቅዱስ ሚካኤልና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ማኅበረ ቅዱስ እስጢፋኖስ ገንዘብ እና አልባሳት ነበሩ።

ከ 1993 ዓ.ም. ጀምሮ ከአጥቢያው ቤተክርስቲያን አስተድዳደር ጋር በገራ ለመስራት ባለመቻሉ ፤ ለአንድ ዓመት ያህል ችግሩን ለመፍታት ጥረት ተደርጎ ከአቅም በላይ በመሆኑ ፤ በ 1994 ዓ.ም. የራሱን የበጎ አድራጎት ክፍል ለመመስረት።

አባላት በአካባቢው መኖር ከጀመሩበት ከ 1984 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ስድስት የሚደርሱ የኔቢጤዎች የዕለት ጉርስ ለመለመን በየዕለቱ በቋሚነት ይመጡ ነበር። ይህ ጉዳይ በቋሚነት የሚከታተል ባላመኖሩ ፤ ለማኅበሩም ሆነ ለተረጂዎቹ አስቸጋሪ እየሆነ ስለመጣ ፤ እራሱን ችሎ በተቋቋመው የበጎ አድራጎት ክፍል እንዲከናወን በማኅበሩ ተወሰነ።

የበጎ አድራጎት ክፍሉም በአንድ ዓመት ውስጥ ከአምሜሪካ እየላኩ የተጠራቀመውንና በቀሲስ አንዱዓለም አስተባባሪነት ከፖርት ላንድ የተላከው እንደመነሻ አድርጎ ፤ ወደ ማኅበሩ እየተመላለሱ ከሚረዱት ስድስት ተመጋቢዎች ላይ 10 በመጨመር ለ 16 ተመጋቢዎች አንድ መጋቢ በመቅጠር በ 1994 ዓ.ም. ትንሳኤ በዓል ጀምሮ በቀን አንድ እንጀራና ወጥ እንዲሰጣቸው እየተደረገ ነው።

ከ 1994 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2001 ዓ.ም. የምግብ ተረጂዎችን ዓይነትና በተለይ አሜሪካ ከሚገኙ የተምሮ ማስተማር ማኅበር አባላት በተከታታይ በተካከው ገንዘብ እስካሁን በማኅበሩ ግቢ ካሉት ቤቶች ፤ ለእንጃራ መጋገሪያና ወጥ መስሪያ አንድ ቤት አስፈቅዶ ፤ ለዚህ ሥራ በተቀጠረችው ሠራተኛ ፤ በየቀኑ በአማካኝነት ለ 20 ተመጋቢዎች እንጀራና ወጥ አዘጋጅቶ ሲሰጥ ቆይቶ ፤ አስተዳደሩ የማዕድ ቤት ጥበት ስለገጠመውና በጎ አድራጎት ዋና ክፍሉም ተረጂዎች ምግብ እስኪወስዱ ማረፊያና አነስተኛ ቢሮ እንዲሁም የንብረት ማስከመጫ ክፈሎች መሥራት ግድ ስለሆነበት፤ አራት ክፍል ቤት በብር 23,822.00 ተሠርቶ በመጠናቀቁ፤ በአሁኑ ጊዚ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል::

ሙሉና ግማሽ ክፍያ ችሎ ስለሚያስተምራቸው ተማሪዎች

ማኅበሩን የሚያውቁ በጎ አድራጊዎችን ተስፋ አድርጎ በ 1994 ዓ.ም. በማኅበሩ የተቋቋመው የበጎ አድራጎት ዋና ክፍል ሥራውን ከመጀምሩ በፊት ፤ የማኅበሩ ትምህርት ቤት ከ 1988 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 37 የሚደርሱ የድሆች ልጆችን በዓመት እስከ ዘጠኝ ሺህ ብር የሚደርስ ወጪ በመሸፈን በነጻና በግማሽ ክፍያ ሲያስተምር ቆይቶ ነበር።

ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ለመምህራን የሚከፍለው ገንዘብ እየተቸገረ በመምጣቱ ፤ የበጎ አድራጎት ዋና ክፍሉ በጎ አድራዎችን በማፈላለግ ወጪውን እንዲሸፍን በደብዳቤ ስለጠየቀ ፤ የበጎ አድራጎት ክፍሉም ትምህርት ቤቱ ወጪያቸውን በመሸፈን ያስተማራቸው 37 ተማሪዎች ዓመታዊ ክፍያ ለመክፈል በወቅቱ አቅሙ ስላልፈቀደለት ፤ በ1997 ዓ.ም. ለ9 ተማሪዎች 2949.20 ብር ከፍሎ በማስተማር የበጎ አድራጎት ሥራውን ጀምሯል።

በ2001 ዓ.ም. ረጂዎች በላኩልን የገንዘብ ዕርዳ በ2000 ዓ.ም. ካስተማርናቸው ላይ የትምህርት እድል ያላገኙ 29 ልጆቸ ጨምረን 43 ተማሪዎች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ተድርጓል፡፡

ቋሚ ረጂ (እስፖንሰር) ስላላቸው ልጆች

የማኅበሩ የበጎ አድራጎት ዋና ክፍል እናት አባት ለሌላቸው ልጆች ቋሚ ረጂ (እስፖንሰር) የማፈላለግ ሥራ የጀመረው፤ በአጥቢያው ወ/ሮ አንጓች ደርበው የሚባሉ ያለ አባት ከሚያሳድጓቸው ሁለት ሴት ሕፃናት ልጆቻቸው ጋር ሲኖሩ፤ ታመው ጥር 30 ቀን 1992 ዓ.ም. በመሞታቸው አባት ነኝ ዘመድ ነኝ የሚል በመታጣቱ፤ ሕፃናቱ ያላሳዳጊ እንዳይቀሩ ከጎረቤት የ6 ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ዓይናለም ደሳለኝ ማኅበሩ በነፃ ካስተማረልኝና የአቅሙን ያህል ከረዳኝ እኔ ከልጆቼ ጋር አሳድጋቸዋለሁ በማለታቸው ሲሆን፡፡ በ1994 ዓ.ም. የማኅበሩ ትምህርት ቤት ከመዋዕለ ሕፃናት (ነርሰሪ) ጀምሮ በነፃ ሲያስተምራቸው ቆይቶ፤ አቅሙ ኖሮን በቋሚነት ባንረዳ ለምን በጎ አድራጊዎችን አናፈላልግም በሚል ሲዊድን ከሚኖሩ ከነዶክተር በላቸው የቤተሰብ ማኅበር ጋር በመነጋገር ከሁለቱ አንዷን ሕይወት ፈቃዱን ለማሳደግ በመምረጣቸው በቋሚነት በሚልኩት ገንዘብ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ የትምህርት ቤት ክፍያ የደንብ ልብስ የትምህርት መሣሪያና ለአሳዳጊዋ በየወሩ የገንዘብ ድጎማ እየተደረገ በአሁኑ ጊዜ የ5ኛ ክፍል ተማሪ ለመሆን በቅለች፡፡

በሕይወት ፈቃዱ የተጀመረው ቋሚ ረጂ (እስፖንሰር) የማፈላለግ ሥራ ቀጥሎ፤ ከቀበሌ አስመስክረው የሚያመጡትን መነሻ በማድረግ፤ እናት አባት ወይም ከሁለት አንዱ የሌላቸውን፣ ወላጆች ቢኖሯቸውም ከልጆች ብዛትና ምንም በቂ መተዳደሪያ ሳይኖራቸው በአካላቸውም የጤና ጉድለት ሠርተው ልጆቻቸውን ለማስተማርም ሆነ ለማሳደግ ያልቻሉትን በማጥናት የመረጥናቸውን ከሀገር ውስጥና ወጪ ላሉ ወዳጆቻችን በተረጂዎቹ ስም የዕርዳ ጥያቄ በማቅረብ፤ በ፳፻፩ (2001) ዓ.ም. ጊዜ እስከ ፳፪(22) የሚደርሱ ልጆች በዓመት ለእያንዳንዳቸው 250 ዶላር የሚልኩላቸው ቋሚ ረጂ (እስፖንሰር) ለማግኘት ችለዋል፡፡

በነፃ የሚማሩ ተማሪዎች በአንድ ቤተሰብ በየዓመቱ በሚላክ የገንዘብ ዕርዳታ የተገዛላቸውን ልብስ ለበስው ጥር 2000 ዓ.ም. በማኅበሩ ት/ቤት
በነፃ የሚማሩ ተማሪዎች በአንድ ቤተሰብ በየዓመቱ በሚላክ የገንዘብ ዕርዳታ የተገዛላቸውን ልብስ ሲሰጣቸው የነበሩ ወላጆች ጥር 2000 ዓ.ም. በማኅበሩ ት/ቤት

የበጎ አድራጎት ዋና ክፍሉ ሙሉ ክፍያ ችሎ የሚያስተምራቸውን የትምህርት ውጤት በተመለከተ

ተማሪዎቹ በቤተሰብ ክትትል ድክመትና አስጠኚ ባለመኖሩ ፤ በአብዛኛው በፈተና ውጤቸው በክፍላቸው ከሚገኙ ተማሪዎች ከግማሽ በታች ያመጡ ሲሆን ፤ በዚህ ሁቤታ ከቀጠሉ ሙሉ ክፍያ እየተከፈላለቸው ተምረው ከጥሩ ደረጃ እንዲደርሱ የታቀደው ግቡን ሊመታ ስለማይችል ፤ በ2000 ዓ.ም. ከአሳዳጊዎቻቸው ጋር ግንኙነት በማድረግና በውጤታቸው ዝቅተኛ የሆኑበትን በማጥናት መፍትሔ ሊፈለግበት እንደሚገባ በተያዘው ዕቅድ መሠረት። ለወላጆች በየጊዜው በቃልና በጽሑፍ በሚሰጥ መመሪያና ማስጠንቀቂያ እንዲሁም ሁለት አስጠኚዎችን በመቅጠር ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ውጤቸውን በማሻሻል ላይ ይገኛሉ።

ለተረጂ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ልብስና የትምህርት መሣርያን ድጋፍ በተመለከተ

የበጎ አድራጎት ክፍሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1994 ዓ.ም. ከአሜሪካ ፖርት ላንድ በቀሲስ አንዱዓለም ይርዳው አሳሳቢነት በወ/ሮ የምስራች አማካኝነት ከተላከው 8000.00 ብር ውስጥ 1839.03 ወጪ በማድረግና ችግረኞች ስለመሆናቸው ከቀበሌ አስመስክረው ላመጡትና ትምህርት ቤቱ ይረዳቸው ለነበሩ 23 ተማሪዎች ፤ የትምህርት ቤት ልብስ (ዩኒፎርም) ማለትም ሱሪ፣ ቀሚስ፣ ሹራብና ሸሚዝ ፤ ለ20 ተማሪዎች በተጨማሪ ቦርሳ ገዝቶ ለልደት በስጦታ መልክ በማበርከት የበጎ አድራጎት ሥራውን ጀምሯል፡፡

የበጎ አድራጊዎችን ዕርዳታ ተስፋ በማድረግ በ1995 ዓ.ም. እና በ1996 ዓ.ም. ለአንድ ተማሪ ለዩኒፎርምና ጫማ በዓመት በአማካይ ብር 150 ለ10 ተማሪ ብር 1500 ለትምህርት መሳሪያ ለቦርሳና ለመጻሕፍት መግዣ ለአንድ ተማሪ በአማካኝ በዓመት ብር 80 ለ10 ተማሪ ብር 800 በግምት ቢይዝም ፤ የተለገስነው ገንዘብ ለዕለት ምግብ ተረጂዎች ምግብ ከማዘጋጃናለተረጂ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ክፍያ ተርፎ የትምህርት ቤት ልብስ ለማሰፈት በቂ ባለመሆኑ ፤ ሳይገዛላቸው ቀርቷል።

የተደረጉ ልዩ ልዩ ጊዜያዊ እርዳታዎችን በተመለከተ

በዚህ መልክ ለሚረዱ በጀት ለመያዝ አስቸጋሪ ቢሆንም ፤ ለታመሙ“ አሳካሚ ለሌላቸው ሌሎች ችግሮችም ላጋጠሟቸው የአካባቢያችን ነዋሪዎች የሚደረግ ጊዜያዊ እርዳታ ሲሆን ፤ እስካሁን የተረዱትን ከዚህ እንደሚከተለው በሠንጠረዥ አቅርበናል።

መቋቋሚያ እየተሰጣቸውና የሚያ ስልጠና አግኝተው ኑሮአቸውን እንዲያሻሽሉ እቅድ የተያዘላቸውን በተመለከተ

ሀ/ በአጥቢያችን የሚገኙ ምዕመናን ብዙዎቹ ሊሰሩና የተሻለ ገቢ በማግኘት ኑሮአቸውን ሊያሻሽሉ ሲችሉ ፤ እንጨትና ቅጠል በመሸጥ የሚያገኙት ገቢ ፤ ለዕለት ጉርስና ለዓመት ልብስ የማይሸፍን ስለሆነ ፤ በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን ለመጦር አቅማቸው ባለመቻሉ ለልመና ተደርገዋል።

ለ/ ልጆቻቸውም የሚለብሱትና የሚመገቡት በቂ መተዳደሪያ ከመቸገራቸውም በላይ ፤ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱት መማር ሲገባቸው ፤ በጎዳና ችግር ተጋልጠው ይገኛሉ።

ሐ/ ሠርተው ኑሮአቸውን ለማሽሽል አውሙ ያላቸውንና የመቋቋሚያ ገንዘብ የተቸገሩትን ፤ ችግኝ በማፍለት፣ ወተት አሰባስቦ ከተማ በመሸጥ፣ በእንጨት የሚሰሩ የእጅ ሥራ ውጤቶችን በመሸጥ፣ ጥጥ በመፍተልና በሽመና ሥራ፣ እንጀራ ጋግሮ በመሸጥና በሌሎችም ሥራዎች ተሰማርተው ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ ፤ የቤተሰቦቻቸውን ችግር ለማቃለል ይቻላል።

መ/ የበጎ አድራጎት ክፍሉም በ1999 ዓ.ም. ለማቋቋሚያ የሚሆን ለአንድ ሰው እስከ 10 ሺህ ብር ከ3 ሰው እስከ 30 ሺህ ብር በዕርዳታ ካገኘ ፤ በገንዘቡ ሥራ ሠርተው ቀስ በቀስ እንዲከፍሉና በተመለሰው ገንዘብ ሌሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ፤ በተከታታይና በተመሳሳይ መርሐ ግብር እንዲረሱበት የማድረግ ፤

ሠ/ ወጣቶችንም በተመለከተ በተመሳሳይ መልኩ በአቅም ማነስ ትምህርታቸውን ያቋረጡ በቀን ወይም በማታ እንዲቀጥሉ ፤ ትምህርታቸውን ጨርሰው ለተቀመጡ ተመሪዎች ፤ የልብስ ስፌት፣ የኮምፒዩተርና የመሳሰሉትን ሙያዎች በማሰልጠን የስራ እድል እንዲያገኙና የመስራት ችሎታው እያላቸው የገንዘብ አቅም አጥተው በሙያቸው ለመጠቀም ያልቻሉ ወጣቶች እንዲቋቋሙ የማድረግ እቅድ አለው። ለዚህም ለሦስት ተማሪዎች ለሙያ ሥልጠና ለአንድ ተማሪ 5 ሺህ ብር ለሦስት ተማሪ 15 ሺህ ብር ያስፈልጋል።

ከዚህ በላይ በፊደል ተራ “መ” እና “ሠ” የታቀዱትን ተግባራዊ ለማድረግ እስካሁን በመርዳት ላይ ለሚገኙ ወዳጆቻችን ከዘገባችን ጋር ጥያቄያችንን ብናቀርብም ምላሽ የሰጡ ባለመገኘታቸው ፤ እስካሁን የዕርዳ ሥራው ሊከናወን አልቻለም፡፡