በትንቢተ ሆሴዕ “ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል፡፡” (ሆሴዕ ፬÷ ፯ (4÷7)) እንዲሁም በግብረ ሐዋርያት ኢትዮጵያዊው ጃንደረባው “የሚመራኝ ሳይኖር ይህን እንዴት ለማወቅ ይቻለኛል?” ብሎ እንደጠየቀ (የሐዋርት ሥራ ፰÷ ፴፩ (8÷31)) ምላሽም እንዳገኘ፤ የአንድነት ኑሮው የገጠሪቱን ቤተክርስቲያን በኅብተሰቡ ቋንቋ የሚያስተምሩ የሰባክያነ ወንጌልን እጥረት ለማቃለል፤ የማሠልጠን ሥራ የጀመረው በ፲፱፻፺ ዓ.ም(1990) ክረምት ሲሆን፤ በወቅቱ በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ብዙ አብያተክርስቲያናት በአገልጋይ እጦት እየተዘጉ፣ ምእመናንም ጠባቂ፣ እረኛ’ መምህር በማጣት በመናፍቃን እየተነጠቁ ስለሆነ፤ የማኅበራችንን የልጅነት ድርሻ ለመወጣት ባለን ዘመናዊ ት/ቤት በክረምት ሲዘጋ ሰባክያነ ወንጌል የማሠልጠኑ ሥራ ተጀምሯል፡፡
በዚህም መሰረት የጽርሐ ጽዮን አንድነት አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን የሰባክያነ ወንጌል ማሠልጠኛ ማዕከል የመሠረት ድንጋይ በብፁዐን አባቶች ቡራኬ በተጣለበት ዕለት፤ አንድ መንፈሳዊ ማሠልጠኛ ያለ ቤተክርስቲያን የተሟላ ስለማይሆን ሠልጣኞች የተማሩትን ሥርዓተ ቤተክርስቲያን በተግባር የሚለማመዱበት፤ የአንድነት ኑሮው አባላት በዓላማቸው በተገለጸው መሠረት ስለ ዓለም ሰላም ለሀገርና ለወገን ደኅንነት የነግህና የሠርክ ጸሎት የሚያደርሱበት ቤተክርስቲያን መቋቋም እንዳለበት ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኑ ለሰልጣኞች የተግባር መለማመጃ እንዲሆንና በዓመት የተወሰኑ ቀናት ብቻ እንዲቀደስበት ብለው በሰጡት መመሪያ መሠረት፤ ይህን መመርያ በመከተል ቤተ ክርስቲያኑ ተቋቋመ፡፡