በማኅበሩ ውስጠ ደንብ አንቀጽ 3 ቁጥር 2 መሠረት የተቋቋመመው ይህ የልማት ክፍል ዓላማው፥

  1. መደበኛ ሥራ የሌላቸውን አባላት በልማት ተግባር እንዲሳተፉ ማደረግ እንዲሁም መደበኛ ሥራ ያላቸውን አባላትና ወጣቶች በትርፍ ጊዜያቸው በልማት ሥራው የሚሳተፉበትን መርሐ ግብር መንደፍ
  2. ከልማት ሥራው የሚገኘው ውጤት ከማሕበሩ ፍጆታ ሲተርፍ ገበያ ላይ እንዲውል ማድረግ
  3. ለልማት ሥራ የሚያስፈልጉ መገልገያዎችና ጥሬ ዕቃዎችን በዕርዳታ የሚያገኝበትን መንገድ ያመቻቻል፣ የተገኘውንም ዕርዳታለተገቢው ሥራ እንዲውል ያደርጋል የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
  4. በተጨማሪም ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በልማት ሥራዎች ተሳታፊ መሆን የአንድነት ኑሮው ዓላማዎች አንዱ በመሆኑ ማኅበሩ ከዚህ በታች የተጠቀሱት የልማት ስራዎች ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።

፩. በትምህርት ዘርፍ

ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ መዋዕለ ሕፃናት በመክፈት በ16 የአንድነት ኑሮው አባላት ልጆች የተጀመረው ት/ቤት ዛሬ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ አድጎ በአነስተኛ ክፍያ ኅብረተሰቡ ለ26 ዓመት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ከ15,000 በላይ የኅብረተሰቡ ልጆች ከዚሁ ት/ቤት ትምህርታቸውን ከመልካም ሥነ ምግባር ጋር አጠናቀው ከከፍተኛ ዩኒቨርስቲዎች ተመርቀው በልዩ ልዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው ሀገራቸውን ቤተሰቦቻቸውንና ራሳቸውን ጭምር እየረዱ ይገኛሉ፡፡

እስከ አሁን ድረስ ከ150 ያላነሱ የአንድነት ኑሮው ውጪ የሚገኙ የኅብረተሰቡ ክፍሎች በዚሁ ት/ቤት በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

፪. በባልትና ሥራ ( የጎጆ ኢንዱስትሪ)

የአንድነት ኑሮው ሠርቶ በሚያገኘው ገቢ መንፈሳዊ አገልግሎቶቹን ለማከናወን እና ኑሮውን መምራት እንዲችል ታስቦ በተቋቋመው የኦቾሎኒ ቅቤ ማምረቻ ከአባላት አልፎ በአካባቢ ለሚኖሩ ከ፸ ለማያንሱ ቋሚና የቀን ሠራተኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

፫. የከብት እርባታና የጓሮ አትክልት

ከከብት እርባታ የሚገኘው ወተት ለቤተሰቡ ልጆችና በከፊል ለሽያጭ ይውላል፤

የከብት እርባታውን ሥራ በገቢ ምንጭነት በስፋት ለማካሄድ ፕሮጀክት ተዘጋጅቶ በተገኘው እርዳታ የማስፋፋት ዕቅዱ ቀጥለዋል፤

ከጓሮ አትክልት የሚገኘው ምርት ለቤተሰቡ የምግብ ፍጆታ ይውላል፤

፬. የወደፊት ዕቅዶች

እግዝአብሔር ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን እንሠራለን ብላችሁ አስቡ እንደተባለው ፤ የአንድነት ኑሮው የውደፊት ዕቅዶች ሰፋ ያሉ ቢሆኑም በአጭር ጊዜ ለማከናወኑ ከታሰቡት ዕቅዶች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

ለማሠልጠኛውና ለአንድነት ኑሮው አገልግሎቶች የገቢ ምንጭነት እንዲያገለግሉ በአንድነት ኑሮው ግቢ ባሉት ክፍት ቦታዎች ሊሠሩ የታሰቡ ከከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት በሳይት ፕላን ፀድቀው የተሰጡ ግንባታዎችን በፍጥነት መጀመር፡፡

የተጀመረውን የሰባክያን ወንጌል ሥልጠና ሥራ ከሦስት ወር ወደ ስድስት ወራት በማሳደግ በክህነት አገልጋይ ላጡ የገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ተደራሽ መሆን፡፡

በአንድነት ኑሮው ዙሪያ ከሚገኙ ምዕመናን ጋር ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት በመፍጠር በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሰላምና ፍቅር የተሞላበት አገልግሎት ለመፈጸም፡፡

የተጀመሩትን የልማት ሥራዎች ባልትናውን ማሳደግና ማስፋፋት በከፍተኛ ትምህርት የተመረቁ የአባላቱን ልጆች በግቢው ውስጥ ሥራ እየተሰጣቸው በሙያቸው እንዲያገለግሉና ተተኪ ሆነው የአንድነት ኑሮውን እንዲረከቡ ጥረት ማድረግ ፡፡