የማኅበራችን የመኖሪያ አካባቢ ከአዲስ አበባ 15 ኪሎ ሜትር የራቀ በመሆኑ ሕፃናትን ወደ ከተማ አጓጉዞ ለማስተማር አስቸጋሪ ስለሆነ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ፈቃድ በመጠየቅ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ መዋዕለ ሕፃናት በመክፈት በ16 የአንድነት ኑሮው አባላት ልጆች የተጀመረው ት/ቤት ዛሬ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ አድጎ በአነስተኛ ክፍያ ኅብረተሰቡ ለ26 ዓመት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ በአካባቢው የግል ት/ቤት ሲከፈት የኛ የመጀመሪያው ከመሆኑም በላይ የኅብረተሰቡን የኑሮ አቅም ያገናዘበ በጣም አነስተኛ ክፍያ ነበር፡፡ ት/ቤቱ ሲከፈት በመዋዕለ ሕፃት የጀመሩት ልጆች ወደ ከፍተኛ ተቋማት ገብተው በልዩ ልዩ የሥራ መስክ ተሠማርተው ይገኛሉ፡፡ የት/ቤቱ የትምህርት አሰጣጥና የተማሪዎች የብሔራዊ የፈተና ውጤት ከሌሎች ት/ቤቶች ጋር ተወዳድሮ የተሻለ በመሆኑ ከፈቃድ ሰጪው የመንግሥት አካል ተደጋጋሚ ሽልማት አግኝቷል፡፡

ከ15,000 በላይ የኅብረተሰቡ ልጆች ከዚሁ ት/ቤት ትምህርታቸውን ከመልካም ሥነ ምግባር ጋር አጠናቀው ከከፍተኛ ዩኒቨርስቲዎች ተመርቀው በልዩ ልዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው ሀገራቸውን ቤተሰቦቻቸውንና ራሳቸውን ጭምር እየረዱ ይገኛሉ፡፡ እስከ አሁን ድረስ ከ150 ያላነሱ የአንድነት ኑሮው ውጪ የሚገኙ የኅብረተሰቡ ክፍሎች በዚሁ ት/ቤት በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በ 2011 ዓ.ም ከ አፀደ ህፃናት እስከ 8ኛ ክፍል በድምሩ 450 ተማሪዎችን ተቀብሎ አስተምሯል፡፡ ተማሪዎች በተመጣጣኝ ክፍያ በማስተማር ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ይሰጣል ፡፡ እግዚአብሔር ቢፈቅድ ትምህርት ቤቱን ወደ 2ኛ ደረጃ የማሰደግ ዕቅድ አለን ፤ ከሴቶች ወጣቶች እና ህፃናት ቢሮ በየዓመቱ (ከ 2005-2011 ) የተላኩ የተቸገሩ 24 ተማሪዎችን ተቀበሎ አስተናግዷል፡፡