የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ (የሐዋርያት) የአንድነት ኑሮ ማኅበርን በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያምና በቅዱሳን አማላጅነት የመሠረተው፤ እንዲሁም በቡራዩ ከተማ ፄዴንያ ስመኝ ማርያም አካባቢ አሁን ማኅበሩ የሚገኝበትን ቦታ መርጦ የአንድነት ኑሮው እንዲጀመር በመንፈሳውያን አባቶች ጸሎትና ቡራኬ ወዶና ፈቅዶ የሰጠው፤ የሰውን ልጆች ድኅነት የሚሻ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

መነሻው ፤ በ፲፱፻፰ ዓ.ም ሲሆን ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰብከተ ወንጌል መስፋፋትና እድገት ስለአስተዳደራዊ መሻሻል ጭምር በመቆርቆር ከአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ፳፰ አድባራት በተውጣጡ ወጣቶች መንፈሳዊያን ማኅበር ተቋቁሞ የነበረው አጠቃላይ ጉባኤ ነው፡፡

ያ ዘመን ሃይማኖት የለሽ የክህደት አስተሳሰብ የሰፈነበት፤ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ቃለ እግዚአብሔርን መማር እንዳይችሉ የተደረገበት፤ ወቅት በመሆኑ በሀገሪቱ የማርክሲዝም የሌኒንዝም ርዕዮተ ዓለም የታወጀበት ፤ ፍልስፍናውም እግዚአብሔር አልባ በመሆኑ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በእምነት ላይ ታላቅ ተጽእኖ ተፈጥሮ የነበረበት ነው፡፡ በተለይም ወጣት ክርስቲያኖች ይህን መቋቋም ባለመቻል ከእምነታቸው እየወጡ ይታዩ ስለነበር፤ ቤተክርስቲያን ተተኪ ትውልድ እንዳታጣ በውስጥና በአፍአ ተጋድሎ መደረግ ስለነበረበት፤ አጠቃላይ ጉባኤውን ይመሩ የነበሩ አባላት፤ በጸሎት በሰጊድ በየገዳማቱ ለዘጉት አባቶች በመንፈሳዊ የጸሎት ኃይል እንዲያግዟቸው በመጠየቅ አብሮ በመቁረብ ባገኙት ዕድል ሁሉ ሌትና ቀን በመወያየት መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸውን ያከናውኑ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የልዑል እግዚአብሔር ረቂቅ ጥበብ ከሰዎች ሕሊና በላይ ልዩና ድንቅ በመሆኑ፤ በሆሣዕና ግዕዛን የሌላቸው ድንጋዮችና ሕፃናት እንዲያመሰግኑ እንዳደረገውወ ሁሉ፤ በዘመኑ በቤተክርስቲያን ጥላ ሥር የተሰባሰቡ ወጣቶች ኃይልና ሞገስ አግኝተው፤ በከሐድያን ነገሥታት ፊት ሳይፈሩና ሳያፍሩ በአደባባይ አምላክነቱን እንዲመሠክሩ ታላቅ ተዓምራቱን የገለጸበት ጊዜ ነበር፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ፤ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው ፡፡›› (፪ኛ ቆሮ. ፲፩፥፳፰) ከማለቱም በላይ ‹‹በከተማው ጣዖት መሙላቱን እየተመለከተ መንፈሱ ተበሳጨበት፡፡›› (የሐ.ሥራ ፲፯፥፲፮) ተብሎ እንደተገለጸው ሁሉ ከእኛ ቀደም የነበሩ የወሊሶው መምህር አባ ወልደ ተንሣይ ግዛው፤ በ`ላ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ፣ ባሕታዊ ገብረ ጊዮርጊስ ትኩነህ፣ አባ ቤተ ማርያም አሽኔ፣ አለቃ ኤልያስ ነቢየ ልዑል፣ መምህር ላቀው ኤዴሳን የመሳሰሉት መንፈሳውያን አባቶቻችን፤ ምእመናን በጣዖት አምልኮ በመናፍቃን ወረራ እንዳይበከሉ፤ በንስሐ ሕይወት እንዲመላለሱ፤ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲስፋፋ፤ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እየተጠናከረ እንዲሄድ ያደረጉት ሐዋርያዊ ተጋድሎ፤ ለዚህ ማኅበር ጥንካሬ አብነት ሆኖታል፡፡

ሆኖም ሥራውን ሲሠራ በሰዎች እና በሁኔታዎች ላይ አድሮ የሚገለጹ በመሆኑ ለምስረታው እንደምክንያት የሚጠቀሱት የሚከተሉት ናቸው፡-

 • ሐምሌ 21 ቀን 1966 ዓ.ም በኢ/ኦ/ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ ጸድቆለት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ 28 ገዳማትና አድባራት ያቋቋሙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የወጣቶችና ጎልማሶች የስብከተወንጌል ማኅበር (አጠቃላይ ጉባኤ)፤
 • ከዚህ ጉባኤ ጋር ግንኙነት የነበራቸው በየሀገረ ስብከቱ የሚገኙ የወጣቶች መንፈሳውያን ማኅበራት፤
 • እንዲሁም መንፈሳውያን አባቶችና በየግላቸው በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሲሳተፉ የቆዩ ምዕመናን በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አጠቃላይ ጉባኤውም በየዓመቱ በተለይም በመስቀል ዋዜማ በሚከበረው የደመራ በዓል፤ ከየአድባራቱ ካህናትና ዲያቆናት ከሚያከናውኑት መንፈሳዊ ዝግጅት በተጨማሪ፤ በአዲስ አበባና በየሀገረ ስብከቱ የሚገኙትን መንፈሳውያን ማኅበራትን በማስተባበር፤ ከአራቱም መአዘን ተነስቶ በዓሉን የተመለከቱ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ መዝሙራት እየዘመሩ’ ትርኢቶችን እያሳዩ ወደ የመስቀል አደባባያቸው በመግባት በወቅቱ የነበረውን የክህደት ትምህርት የሚቃወሙ መንፈሳዊ ዝግጅቶች በግልጽ እያቀረቡ ሃይማኖታዊ ምሥክርነታቸውን ይሰጡ ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት በጊዜው የነበሩ የርዕዮተ ዓለሙ አራማጆች የክህደት ትምህርታቸውን በወጣቱ ላይ እንደሚፈልጉት ማስፋፋት ባለመቻላቸው፤ ክርስቲያን ወጣቶች በመንፈሳዊ ማኅበር እንዳይደራጁ ተጽእኖ በመፍጠር፤ በሀሰት ላይ የተመሠረቱ ክሶችንና የስም ማጥፋት ውንጀላዎችን በማካሄድ እንቅስቃሴውን ለመግታትና ማኅበሩን ለማዳከም ሙከራቸውን ቀጠሉ፡፡ የአጠቃላይ ጉባኤው አባላትም ከተለያዩ የመንፈሳውያን ማኅበራት የተውጣጡ እና መንፈሳዊ ጽናታቸውም አንድ ዓይነት ባለመሆኑ፤ የፖለቲከኞቹን ተጽዕኖ መቋቋም በላመቻላቸው አጠቃላይ ጉባኤው በመንግሥት ትዕዛዝ ግንቦት 5 ቀን 1972 ዓ.ም እንዲዘጋ ተደረገ፡፡

ቀደም ሲል ይህንኑ በመፍራት ማኅበሩ ቢፈርስ እንኳ የተጀመረውን ዓላማ ማስቀጠል እንዲቻል ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ በህቡዕ የተመሠረተውና በመጀመሪያ በታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም ኋላም በየግል መኖሪያ ቤት ውስጥ ይካሄድ የነበረው የማኅበረ መድኃኔዓለም ደብረ ዘይት ማኅበር ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ አሠረ ሐዋርያት በሚል ስያሜ ማኅበር አቋቁሞ፤ የደመራ በዓል በተለመደው ሁኔታ በድምቀት እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ አሠረ ሐዋርያት ተብሎ የተሰየመውም፤ ቀድሞ በእነመምህር አባ ገብሥላሴ ተድላ ተጀምሮና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ተዘግቶ የነበረው ማኅበረ ሥላሴን መታሰቢያ ያደረገ በየወሩ ለ7 ቀራቢ በሆነው እሑድ የሚሰበሰብ ነበር፡፡

የሀገሪቱ መሪዎች ይከተሉት የነበረው የሶሻሊዝምና ኮሚኒዝም አስተሳሰብ እያደገ፤ በቤተክርስቲያን አስተዳደርና በምእመናን እንዲሁም በወጣቶች ላይ የሚያደርገው ተጽዕኖ እየተጠናከረ በመምጣቱ፤ የማኅበረ ደብረ ዘይት አባላት በየግል እየኖርን ለቤተክርስቲያን ከምናበረክተው አገልግሎት ይልቅ፤ በአንድ ላይ ቤት ሠርተን ሀብትና ንብረታችንን አዋህደን በመኖር የምናበረክተው የበለጠ ይሆናል የሚል ሀሳብን አመንጭተው፤ የአንድነት ኑሮውን ለመመሥረት ከስምምነት ላይ በመድረሳቸው ማኅበረ ደብረ ዘይት ከተመሠረተበት ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ የአንድነት ኑሮውን ሀሳብ በተግባር ለመተርጎም ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተው፤ በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ዓላማ ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ የሚያጠኑ 5 የኮሚቴ አባላት ሐምሌ 26 ቀን 1979 ዓ.ም ተመረጡ፡፡

እነዚህ አባላትም ኅዳር 26 ቀን 1980 ዓ.ም በተደረገው የማኅበረ ደብረ ዘይት ወርኃዊ ስብሰባ የአባላቱን የምርጫ ሥርዓት የሚያረጋግጥ ቅጽ እንዲታደል አድርገው ጥር 6 ቀን 1980 ዓ.ም 21 አባላት ያለማንም ተጽዕኖ ወደው ፈቅደው በአንድነት ኑሮው ለመኖር መስማማታቸውን አረጋገጡ፡፡

የአንድነት ኑሮውን አባላት ቁጥር ለማሳደግ እንዲቻል ወደ በአሠረ ሐዋርያት ላሉና ወደ ደብረ ዘይት ለመግባት ደጅጥናት ላይ ለነበሩ የዚህ ምርጫ ቅጽ እንዲሰጣቸው ተደርጎ እሰከ 57 የሚደርሱ የአንድነት ኑሮውን መረጡ፡፡ የካቲት 23 ቀን 1980 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ የማኅበሩን ስም ጽርሐ ጽዮን ሞዴል የመኖሪያ ቤት የኅብረት ሥራ ማኅበር የሚል ስያሜ ተሰጥቶት መተዳደሪያ ደንብ ተቀርጾ ለጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ እንዲጸድቅ ተደረገ፡፡ መተዳደሪያ ደንቡም ለከተማ ልማት ቤት ሚኒስተርም ቀርቦ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ እንዲንቀሳቀስ ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡

አባላቱም ለወንጌል አገልግሎት አንድ ላይ መኖር በወቅቱ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ስላመኑበት፤ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን ዕውቀትን ጉልበትንና ሀብትን አንድ ላይ በማድረግ መንፈሳዊውንና ቁሳዊውን በማዋሐድ ዓላማውን በተግባር ለመፈጸም ተነሣሥተው የቤቶችን ግንባታ ሁሉንም በአንድ ላይ ለማጠናቀቅ ባለመቻሉ፤ የአራት አባወራ መኖሪያ የሚሆን አንድ ሕንፃ ስለተጠናቀቀ ኅዳር ፳፯(27) ቀን ፲፱፻፹፬(1984) ዓ.ም. በ፱(9) አባላት አንድነት ኑሮው ተጀመረ፡፡

የአንድነቱ ኑሮ መሥራችና አጠናካሪ ማኅበረ ደብረ ዘይት

አጠቃላይ ጉባኤ ከመዘጋቱ አስቀድሞ ይህ ችግር እንደሚከሰት የተረዱ አንድ አንድ የአመራሩ አካላት፤አጠቃላይ ጉባኤው ቢፈርስ እንኳንዓላማውና አገልግሎቱ በየሰንበት ት/ቤቱ ዘላቂነት እንዲኖረው ፤ ማኅብ ደብረ ዘይትን በማቋቋም በየቤተ ታቸው በየወሩ በመሰባሰብ ጸሎት በማድረግ እንዲመካከሩ፤ ወጣቶች በዓላማቸው ጸንተው አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ያደርጉ ነበር፡፡

አሠረ ሐዋርያት

አጠቃላይ ጉባኤው ከፈረሰ በኋላ ማኅበረ ደብረዘይት 1973 ዓ.ም ለአጠቃላይ ጉባኤ ድጋፍና ይቅርብ ተሳትፎ ከነበራቸው በቁጥር 50 የሚደርሱ ወጣቶችን አሠረ ሐዋርያት በሚል ስያሜ በማኅበር በማሰባሰብ ሕያው እግዚአብሔር በከበረ ደሙ ለመሠረታት ቤተ ክርስቲያን በሙሉ ልብ ለማገልገል እንዲሁም ከራስ አልፎ ለሌላው ለመትረፍ በአንድ ሃሳብ በመስማማት በአጠቃላይ ጉባኤ ፤

የአንድነት ኑሮ

የማኅበረ ደብረዘይት አባላት ከብዙ ፈተናና የሐሳብ ውጣ ውረድ በኋላ ለአገልግሎት አመቺ ይሆን ዘንድ በአንድነት እንኑር ወይስ በጉርብትና ወይስ በያለንበት እንኑር በሚሉ በሦስት ሐሳቦች ለረጅም ጊዜ ሲመክሩና ሲጸልዩ ቆይተው፡-

 • ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለየብቻ መኖር ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ፤
 • በጉርበተና መኖር ሥጋዊ ውድድርን እንደሚያመጣ ፤
 • በአንድነት መኖር እንደ ሐዋርያት ለአገልግሎት እንደሚያ ተጋ፤ በዓለም ላይ ያለውን ሥጋዊ ሐብት አግኝቶ ተረዳድቶ ለመኖር እንቅፋት እንደማይሆን ተማምነው የካቲት 3 ቀን 1980 ዓ.ም የቅዱሳንን ፈለግ በመከተል የአንድንት ኑሮውን ለመመሥረት ከማኅበረ ደረዘይትና ከአሐሠረ ሐዋርያት ወሰኑ፡፡

ሞዴል የሕብረት ሥራ ማኅበር

ከማኅበረ ደብረዘይትና ከአሠረ ሐዋርያት እንዲሁም በደጅ ጥናት ከነበሩር አባላት መካከል በቀረበላቸው ነፃ ምርጫ የአንድነት ኑሮውን የመረጡ 50 የሚደርሱ አባላት መጋቢት 28 ቀን 1980 ዓ.ም በአደረጉት ስብሰባ ‹‹ ጽርሐ ጽዮን የመኖሪያ ቤት ሕብረት ሥራ ማኅበር ›› የሚል ማኅበር መሥርተው ለከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር በማቅረብ ፈቃድ አግኝተዋል፡፡ በታሪክ ልዩ መልክ ያለው ማኅበር በመሆኑ ሞዴል የሚል ስም ተሰጥቶት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

ስያሜ

‹‹ ጽርሐ ጽዮን ›› ማለት ‹‹ የጽዮን አዳራሽ›› ማለት ሲሆን ስሙም የተወሰደው የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ተቀብላ የምትጠራው ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉባት የማርቆስ እናት ቤትን ያመለክታል፡፡ለዚያ መታሰቢያ እንዲሆን ማኅበሩ ጽርሐ ጽዮን ተብሏል፡፡

እነሆ ዛሬ በማኅበሩ ዙሪያ የሚገኘው ‹‹ መደ ቢሻን›› ተብሎ የሚጠራው መኖሪያ ሠፈር ስያሜውን ከማኅበሩ በመውሰድ ‹‹ጽርሐ ጽዮን›› መንደር በሚል እየተጠራ ይገኛል፡፡

የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ

ይህ ማኅበሩ የተረከበው የይዞታ ቦታ ቀደም ሲል የፄዴንያ ስመኝ ማርያም ታቦት ያድርበት እንደነበርና ወደፊት በቦታው ላይ የእግዚአብሔር ሰዎች ይኖሩበታል ብለው አባቶች ትንቢት ይናገሩ እንደነበር ፤ የገዳሙ አገልጋይ የነበሩት አባ ወልደ ዮሐንስ ለማኅበሩ ሦስት አባላት ጠርተው አሳውቀዋል፡፡

ማኅበሩ መኖሪያ ቤት የሚሠራበትን ቦታ ከሸዋ ከተማ ልማት 41 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ተረክቧል፡፡ ቤቱቹን ለመሥራት የሚያስችል የገንዘብ አቅም ስላልነበረ ከከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር በተጻፈልን የድጋፍ ደብዳቤ ከቤቶች እና ቁጠባ ባንክ የብድሩን መስፈርት ማሟላት በሚችሉ በ20 አባላት ስም ብር 258,731 /ሁለት መቶ ሃሣሳ ስምንስ ሺህ ሰባት መቶ ሰላሳ አንድ ብር/ ለመበደር ጥቅምት 8 ቀን 1982 ዓ.ም የብድር ውል ስምምነት ፈጽመዋል፡፡

የመጀመሪያ ክፍያ ከባንክ እንደተገኘ የመኖሪያ ቤቶችን ለመሥራት ቦታው ላይ የነበረውን የባሕር ዛፍ ጉቶ የማስነቀልና የመደልደል ሥራ ተከናውኗል፡፡ በዚህም መሠረት የካቲት ፲(10) ቀን ፲፱፻፹፪(1982) ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጡ በዓሉ በድምቀት ተከብሯል፡፡ በዕለቱም

ከቅዱስ ሲኖዶስ

 • ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ
 • ብፁዕ አቡነ ኤልያስ

ከከተማ ልማት

 • ሚኒስትሩ ጓድ ታደሰ ኪዳነ ማርያም
 • የመምሪያ ኃላፊዎች
 • ለቤቶች ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የመንግሥት እና የድርጅት ኃላፊዎች
 • የአካባቢ ታዋቂ ግለሰቦች

የማኅበሩ አባላት ቤተሰቦች ተገኝተው በዕለቱ ታልቅ የምስጋና በዓል ተደርጓል።

የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ‹‹ልማተ ከተማ›› መጽሔት መስከረም 1982 ልዩ ዕትም ገጽ 20 እና 21 የማኅበሩን የመኖሪያ ቤትና የሁለገብ አዳራሽ ንድፍ ፕላን ጋር ‹‹እውን ይሆን ይሆን?›› በሚል ርዕስ ‹‹የተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር በአዋጅ ከተቋቋመበት ጀምሮ በርካታ የሆኑ ልዩ ልዩ ማኅበራትን በማደራጀት ኅብረተሰቡ የራሱ መኖሪያ ቤት ባለቤት እንዲሆን ጥረት አድርጓል፡፡ በዚህ የማይናቅ ጉዞ ውስጥ ለምሳሌነት የሚጠቀሱ አያሌ ማኅበራት ተፈጥረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በዓይነቱ ልዩ የሆነና ለሀገራችንም ሆነ ለመላው ዓለም በሞዴልነት የሚጠቀስ ‹‹ጽርሐ ጽዮን ሞዴል›› የተባለ የኅብረት ሥራ ማኅበር ብቅ ብሏል፡፡ ይህ ማኅበር በአደረጃጀቱ እስከአሁን ካሉት ማኅበራት የተለየ በመሆኑ እንደ ጅምሩ መጨረሻውን ለማየት በጉጉት እንጠብቃለን›› የሚለውን መልዕክት አስፍሯል፡፡

የአንድነት ኑሮ ሲጀመር

ለመጀመሪያ ጊዜ በተሠሩት አራት መኖሪያ ቤቶች ለመግባት ተዘጋጅተው ይጠብቁ የነበሩ 9 አባላት ኅዳር 27 ቀን 1984 ዓ.ም የጋራ ኑሮውን ጀምረዋል፡፡

አባላት ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ቡራዩ በመጡበት ሰዓት፤ መብራት፣ ውኃ፣ መጓጓዣ፣ መገናኛ ስልክ የመሳሰሉት የመሠረተ ልማት አውታሮች ያልተዘረጉበት ሰዓት በመሆኑ ከፍተኛ ችግር ገጥሞአቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዕለት በዕለት ያሳስባቸው የነበረው የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ስለነበር፤ የጎደላቸውን እንዲያ ሞላላቸው ወደ ፈጣሪያቸው በጸሎት እየተማጸኑና በምስጋና እየዘመሩ በፍቅርና በደስታ ይኖሩ ጀመር፡፡ ከወራትና ከዓመታት በኋላ ጥያቄያቸው ሁሉ መልስ አግኝቷል፡፡

አባላቱ የአንድነት ኑሮውን ለማቋቋም በወሰኑበት መጋቢት 28 ቀን 1980 ዓ.ም ቀርቦ የነበረው ዓላማ ከዚህ የሚከተለው ሲሆን፤ እምነት ተስፋ ፍቅራቸውን በእንዲህ ዓይነት እምነትና ምስጋና እየገለጹ እስካሁን ልዩ ልዩ ፈተናዎችን በልዑል እግዚአብሔር ቸርነት በወላዲተ አምላክ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ቃል ኪዳን በቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነትና በጻድቃን በሰማዕታት አማላጅነት በጽናት ለመኖር በቅተዋል፡፡

የማኅበሩ ዐበይት ዓላማዎች

 • አባላት ያላቸውን ሥጋዊና መንፈሳዊ ሀብት በማዋሐድ እርስ በርስ በመረዳዳትና በመደጋገፍ፣ በሰላምና በፍቅር በአንድነት በመኖር ለኅብረተሰቡ አርአያና ምሳሌ ለመሆን፣
 • በኢ.ኦ.ተ. ቤተክርስቲያን ስብከተወንጌልን ለማስፋፋት በሚደረገው አገልግሎት ለቤተክርስቲያን እድገትና ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት፣
 • ለሀገር ፍቅርና ለወገን ክብር ክርስቲያናዊ ድርሻን ለማበርከት፣
 • ከክርስትና እምነት ውጪ የሆኑ ጎጂ ባህሎችን በማስወገድ፤ ለመላው ኅብረተሰብ አርአያና ምሳሌ ለመሆን፣
 • በልዩ ልዩ ችግሮች ላይ የወደቁትን የሰው ልጆች፣ ይልቁንም የሃይማኖት ወገኖች ለመርዳት፤
 • በአንድነት ኑሮው አካባቢ ካለው ኅብረተሰብ ጋር፤ እንደሁኔታው የደስታ የኀዘንና የልማት ተግባር ሁሉ በጉልበትም በገንዘብም ተሳትፎ ለማድረግ፤
 • በምድር ላይ ቸነፈርና ረሀብን የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲደርሱ፤ የጸሎት፣ የሐሳብ፣ የጉልበትና የገንዘብ እርዳታ ለማድረግ የሚሉ ናቸው፡፡

የአንድነት ኑሮው ለሚያደርገው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲ ያን መ/ፓ/ጠቅላይ ጽ/ቤት እንዲሁም በሥጋዊ ኑሮው ከመንግሥት አካላት፣ ከአካባቢው አስተዳደርና ኅብረተሰብ ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ቀደም ሲል ከፍትሕ ሚኒስቴር በቁጥር (፲፩፻፵፩)1141 ጳጉሜን ፬(4) ቀን ፲፱፻፺፭(1995) ዓ.ም. አሁን ደግሞ ከፌዴራል የሰላም ሚኒስቴር ሕጋዊ እውቅናን አግኝቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

የማኅበሩ አቋም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምታምንበትን ዶግማ፣ የተቀበለችውን ሥርዓት (ቀኖና) ያምናል ይቀበላል፡፡ የማንኛውም የፖለቲካ፣ የዘርና የጎሳ ድርጅት አባል አይሆንም፡፡

ለማኅበሩ ምሥረታ በአርዓያነት የሚጠቀሱ አባቶች

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።” ከማለቱም በላይ በአቴና ከተማ ሳለ ጣዖት መሙላቱን እየተመለከተ መንፈሱ ተበሳጨበት። ተብሎ እንደተገለጸው ሁሉ፤ ከኛ ቀደም የነበሩ የወሊሶው መምህር አባ ወልደተንሣይ ግዛው፤ በኋላ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ’ አባ ገብረሥላሴ ተድላ’ ባሕታዊ ገብረጊዮርጊስ ትኩነህ’ አባ ቤተማርያም አሽኔ’ አለቃ ኤልያስ ነቢየ ልዑል’መምህር ላቀው ኤዴሳን የመሳሰሉ መንፈሳውያን አባቶቻች፤ በማኅበረ ደብረዘይት ውስጥም ከመነኮሳት መካከል ብንጠቅስ የበዓታው ቅዳሴ መምህር አባ ይትባረክ ወልደሥላሴ’ የደብረ ዓሚን ተክለሃይማኖት አለቃ የነበሩት መልአከ ዓሚን ዘካርያስ ኃይለማርያም በኋላ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ይገኙበታል፡፡

ምእመናን በጣዖት አምልኮ በመናፍቃን ወረራ እንዳይበከሉ፤ በንስሐ ሕይወት እንዲመላለሱ፤ የስብከተወንጌል አገልግሎት እንዲስፋፋ፤ የቤተክርስቲያን አገልግሎት እየተጠናከረ እንዲሄድ ያደረጉት ሐዋርያዊ ተጋድሎ፤ ለዚህ ማኅበር ምሥረታ መነሻ ሆኖታል፡፡

የወሊሶው መምህር አባ ወልደ ተንሣይ ግዛው፤ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ

ባሕታዊ ገብረ ጊዮርጊስ ትኩነህ

 

ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ

መምህር ላቀው ኤዴሳን