ማሠልጠኛው “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጽርሐ ጽዮን አንድነት አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን የሰባክያነ ወንጌል ማሠልጠኛ ማዕከል” ተብሎ ይጠራል፡፡
በትንቢተ ሆሴዕ “ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል፡፡”(ሆሴዕ ፬÷፯ ) እንዲሁም በግብረ ሐዋርያት ኢትዮጵያዊው ጃንደረባው “የሚመራኝ ሳይኖር ይህን እንዴት ለማወቅ ይቻለኛል?” ብሎ እንደጠየቀ(የሐዋርት.ሥራ ፰÷፴፩) ምላሽም እንዳገኘ፤ የአንድነት ኑሮው የገጠሪቱን ቤተክርስቲያን በኅብተሰቡ ቋንቋ የሚያስተምሩ የሰባክያነ ወንጌልን አጥረት ለማቃለል፤ የማሠልጠን ሥራ የጀመረው በ፲፱፻፺(1990) ዓ.ም. ክረምት ሲሆን፤ በወቅቱ በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ብዙ አብያተክርስቲያናት በአገልጋይ እጦት እየተዘጉ፣ ምእመናንም ጠባቂ፣ እረኛ’ መምህር በማጣት በመናፍቃን እየተነጠቁ ስለሆነ፤ የማኅበረችንን የልጅነት ድርሻ ለመወጣት ባለን ዘመናዊ ት/ቤት በክረምት ሲዘጋ ሰባክያነ ወንጌል የማሠልጠኑ ሥራ ተጀምሯል፡፡
ሥልጠናውን ሲጀመር ከፄዴንያ ስመኝ ማርያም ገዳም ጋር በመተባበር በገዳሙ ጽ/ቤት የተከናወነ ሲሆን፤ አዳራቸውና ምግባቸው በዘመናዊ ትምህርት ቤታችን በእንጨት ከተሠራ ተደራራቢ አልጋ ወደ ብረት አልጋ እስኪለወጥ ለሦሰት ዓመት ቀጥሎ ነበር፡፡
በክረምት ወራት ተጠብቆ በሚሰጠው ሥልጠና የመምህራነ ወንጌልን እጥረት ማስወገድ ስለማይቻል ዓመቱን በሙሉ ማካሄድ እንዲቻል “ኑ እና እዩ” በሚል መሪ ቃል ማኅበሩ ከምእመናን ጋር የተገናኘበት የመጀመሪያው የእግር ጉዞ መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የከፋ ሸካ ቢንች ማጂ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፤ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ፣ የወላይታና ዳሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ በተገኙበት የማሠልጠኛው ሕንፃ የመሠረት ድንጋይ፤ የአንድነት ኑሮው ከይዞታው በመደበው ፬(4) ሺህ ካ.ሜ ቦታ ላይ ግንቦት ፳፪(22) ቀን ፲፱፻፺፮(1996) ዓ.ም. ተቀመጠ፡፡